🔇Unmute
ይርጋ ጨፌ፤ሕዳር 10/2018 (ኢዜአ)፡-በሌማት ትሩፋት መርሀግብር የቤተሰብ የምግብ ፍጆታን ከመሸፈን ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን ይርጋ ጨፌ ከተማ በልማቱ የተሰማሩ ማህበራት ገለጹ።
በከተማው መርሀግብሩን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በማስተሳሰር ከ6 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

ከሦስት ዓመት በፊት በአርባ ምንጭ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሀግብር በምግብ ሉአላዊነትን ማስከበርና ክብርን ከማረጋገጥ ጋር የተያያዘ ነው።
ዓላማውም በሥጋ፣ በእንቁላል፣ በማርና ወተት የተትረፈረፈ ምርት በማምረት መጠቀምና የገቢ ምንጭ ማድረግ ነው።

መርሀግብሩ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በልማቱ የተሳተፉ በርካቶች ተጠቃሚ እየሆኑ መጥተዋል።
በጌዴኦ ዞን ይርጋ ጨፌ ከተማም በመርሀግብሩ የተሳተፉ ማህበራት ከዘመናዊ እንስሳት እርባታ እና ንብ ማነብ ሥራቸው ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ነው የገለጹት።
በመርሀግብሩ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ አቅርቦትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለአካባቢ ገበያ በማቅረብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል አቶ አበባው አዳነ፤ በተሻሻሉ የወተት ላሞች እርባታ እና በንብ ማነብ ዘርፍ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

ከአርባ በሚበልጡ ዘመናዊና ባህላዊ የንብ ቀፎዎች የሚያመርቱትን ማር ከቤት ውስጥ ፍጆታ አልፈው ለገበያ በዓመት ከ35 ኪሎ ግራም በላይ የተጣራ ማር እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ከዘጠኝ የተሻሻሉ ላሞች በቀን ከአንድ ላም ብቻ በአማካይ እስከ 15 ሊትር ወተት እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
ከልማት ሥራው ተጠቃሚ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለአምስት ሰዎች የሥራ እድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ከመንግስት ባገኙት የ150 ሺህ ብር ብድር አምስት ሆነው በአንድ ቀን የዶሮ ጫጩት እርባታ ሥራ እንደተሰማሩና ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን የገለጸው ደግሞ የብቁ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ድጋፌ ተፈሪ ነው።

ከአስር ሺህ በላይ የአንድ ቀን ጫጩቶችን በመረከብ 45 ቀን ሲሞላቸው ለሽያጭ በማቅረብ ትርፋማ መሆናቸውን ተናግሯል።
በአሁኑ ወቅት የተበደሩትን ገንዘብ ከመመለስ ባለፈ ከ125 ሺህ ብር በላይ በባንክ ተቀማጭ ማድርጋቸውን ተናግሯል።
የሌማት ትሩፋት መርሀግብር በአካባቢያቸው ያለውን ጸጋ ተጠቅመው እንዲለወጡ እድል መፍጠሩን የተናገረው ደግሞ የድል በትግል የንብ አናቢ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ኤርሚያስ ጥላሁን ነው።

በተለይ በይርጋጨፌና አካባቢው በጥምር ግብርና ቡና የሚመረት መሆኑ ለንብ ማነብ ሥራ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንና በዘርፉ ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን ተናግሯል።
ከዘመናዊ የንብ ቀፎዎች ከ500 ኪሎ ግራም በላይ ድፍድፍና የተጣራ ማር ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሶ በቀጣይ በንግስት ንብ ብዜት ሥራ የመሰማራት ዕቅድ እንዳላቸው ጠቁሟል።
የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዮሴፍ አየለ በበኩላቸው፤ በከተማው በሌማት ትሩፋት በተለይም በማር፣ በወተትና በዶሮ እርባታ ከ20 በላይ ማህበራት ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ለማህበራቱ በተመቻቹ ሼዶች ምርቶቻቸውን ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸው፣ የሌማት ትሩፋት ስርዓተ ምግብን ከማሻሻል በተጨማሪ የእንስሳት ተዋፅኦ ምርታማነትን እያሳደገው መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
በተያዘው ዓመት ብቻ ከ2 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የተጣራ ማር ለገበያ መቅረቡን የተናገሩት አቶ ዮሴፍ፣ መርሀግብሩ ገበያን ለማረጋጋት እያገዘ መሆኑንም ተናግረዋል።
ልማቱን ለማጠናከር ዘንድሮ ከ6 ሺህ በላይ ወጣቶችን በዘርፉ ለማሰማራት የወጣቶች ልየታ፣ የመስሪያ ቦታና የብድር አቅርቦት መመቻቸቱንም አስታውቀዋል።
አዶላ ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በበልግ አዝመራ ከ260 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ...
Apr 9, 2026
ጎንደር፤ መጋቢት 24/2018( ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ከ239 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በከተሞች የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ ተ...
Apr 3, 2026
ደብረ ማርቆስ፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ):-በምስራቅ ጎጃም ዞን ገበያውን ለማረጋጋት ከ169 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ የህብረት ሥራ...
Mar 31, 2026
ሀዋሳ፤ መጋቢት 16/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተኪ ምርት የማምረት አቅም በማሳደግ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን አምራ...
Mar 26, 2026