ሚዛን አማን፣ሐምሌ 16/2017 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ልማት ሥራዎች በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚያፋጥኑ ተገለጸ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ለኢዜአ እንደገለጹት በምግብ ራስን መቻል የሕልውና ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ሊረጋገጥ የሚችለው ከተረጂነት መላቀቅ ሲቻል ብቻ መሆኑን ያነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ መንግስት ይህን ለማሳካት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤት እያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል።
በክልሉም ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዘንድሮ ከ5 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴ እና ከ36 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ሩዝ መልማቱን ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል በክልሉ ሩዝና ስንዴ ማልማት እንዳልተለመደ አስታውሰው፣ ለክልሉ አርሶ አደሮች አዳዲስ ሰብሎችን በማስተዋወቅ በምግብ ራስን ለመቻል ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ክልሉ ለግብርና ሥራዎች ያለውን ምቹ የአየር ጸባይ ተጠቅሞ በሁሉም የሰብል አይነቶች ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ማስረሻ አንስተዋል።
ዘንድሮ እንደ ክልል ከ750 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ20 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ምርት የማምረት ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸው ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።
በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን የጉራፈርዳ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ተስፋ አማን ሩዝን በኩታገጠም በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረው፣ ለዚህም መንግስት የሰጠው የልማት አቅጣጫ ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።
በዘንድሮ በበልግ እርሻ በሁለት ሄክታር ማሳ ላይ ካለሙት የሩዝ ማሳ ከ70 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ተገቢ እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሩዝ፣ በቆሎና ሌሎች ሰብሎችን በማልማት ለምግብ ፍጆታ ከማዋል ባሻገር ለገበያ በማቅራብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን የተናገሩት ሌላው የወረዳው አርሶ አደር ጉችዬ ተመስገን ናቸው።
ዘንድሮ የተሟላ ግብዓት ተጠቅመው ካለሙት የእርሻ ማሳ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
በክልሉ በተለያዩ አማራጮች እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ሥራዎች የበርካታ ዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ ባለፈ በምግብ ራስን የመቻል እሳቤን ለማረጋገጥ እያገዙ መሆናቸው ተመላክቷል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ የቁልፍ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ አዋጅን ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስ...
Feb 28, 2025
ደሴ፤ የካቲት 16/2017 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ወሎ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓሊ መኮንን ገለ...
Feb 24, 2025
አሶሳ ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ):- የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ችግር ፈቺ ስራዎችን እንዲያከናውኑ እየተሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ የልማት ትስስርና የኢኮኖሚ ውህደት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ የአፍሪካ ቀንድ...
Feb 12, 2025